“ከግጭት አዙሪት ወጥቶ ወደ ሰላም ከፍታ ለመሻገር የሁላችን ርብርብ እና መደማመጥ ያስፈልጋል” ኮሎኔል ኤፍሬም ተስፋየ

36

ባሕርዳር፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሁለንተናዊ እና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል” በሚል መሪ ሀሳብ በባሕርዳር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋሁን ድረስ በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመወያያ ሀሳብ አቅርበዋል። አቶ ተስፋሁን የተፈጠረው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ኑሮ ያናጋ በተለይም ደግሞ አርሶ አደሩ ወቅቱን ጠብቆ የማምረት ሥራውን እንዳያከናውን ያስተጓጎለ ነው ብለዋል።

አቶ ተስፋሁን የአማራ ሕዝብ የወሰን እና የማንነት፣ የሕገ መንግሥት፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመሥራት፣ የፍትሐዊነት እና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች ያሉት ቢኾንም ጦርነትን እንደመፍትሄ መቁጠር ግን ተገቢ አለመኾኑን አስረድተዋል። ይልቁንም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመኾን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በሆደ-ሰፊነት መታገል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አቶ ተስፋሁን ልዩነት ያላቸው አካላት የክልሉን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ንግግር መመለስ አለባቸውም ብለዋል። በፍፁም ሰላማዊነት መነጋገር ሲገባ በትጥቅ የተደገፈ ትግል ውስጥ ተገብቶ የሕዝብን ደኅንነት ማወክ ትክክለኛ አማራጭ አለመኾኑንም ጠቁመዋል። አሁንም ቢኾን ግጭትን በማስወገድ አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነት መቀነስ እና የክልሉን ኢኮኖሚም ከውድመት መታደግ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እና ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ተወያዮች እንዳሉት፦

👉 የሕዝብን ጥያቄ የመፍታት አቅም፣ ፍላጎት እና ቅንነት ያለው አመራር በመፍጠር ሕዝብን መካስ ያስፈልጋል
👉 ኢትዮጵያ በዘር ከመገፋፋት እና ከመጠቃቃት ነጻ የኾነች ፣ዜጎች በሁሉም ቦታ እኩል የሚስተናገዱባት ሀገር እንድትኾን ማድረግ ያስፈልጋል።

👉 የፌዴራል መንግሥት የአማራ ሕዝብ ኅብረ ብሔራዊ እና ልማት ወዳድ እንጅ ጦርነትን የማይፈልግ መኾኑን በውል በመገንዘብ የሕዝቡን ተዘዋውሮ የመሥራት እና የደኅንነት መብት ያስጠብቅ።

👉ግጭትን ለማባባስ የሚጥሩ ግለሰቦች እና ሚዲያዎች ለሕዝብ ሰላም ማሰብ እና ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው።
👉 የተቀመጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን የሰላም ሁኔታ እየገመገመ የሚሻሻል መኾን አለበት።
👉 ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት ጠንካራም ሆደ ሰፊም አመራር መስጠት አለበት።
👉 የአማራ ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመኾን በኩል በተግባር የተፈተነ ታሪክ ያለው ነው። ከዚህ እውነታ በሚቃረን ሁኔታ ሠራዊቱን ከአማራ ሕዝብ ለመነጠል የሚሠራ አሻጥር በፍጥነት መቆም አለበት ሲሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች አስተባባሪ ኮሎኔል ተስፋየ ኤፍሬም የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሕግ በተቀመጠለት ተልዕኮ መሰረት እና በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚንቀሳቀስ ነው ብለዋል። “ሠራዊቱ የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ከማስጠበቅ የዘለለ ሌላ አጀንዳ የለውም” ሲሉም ተናግረዋል። ለሠራዊቱ ደጀን እየኾነ ታሪካዊ ውለታ ሲከፍል የኖረው የአማራ ሕዝብ ሰላሙ በዘላቂነት እንዲከበር በትኩረት እንሠራለንም ብለዋል። የክልሉ ሰላም ተገምግሞ መሻሻል የሚያሳይ ከኾነ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊነሳ እንደሚችልም አመላክተዋል።

ኮሎኔል ተስፋየ “ከግጭት አዙሪት ወጥቶ ወደ ሰላም ከፍታ ለመሻገር የሁላችን ርብርብ እና መደማመጥ ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል። አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን በመምከር ለሀገር ሰላም መቆም እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!