“ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት ተመዝግበዋል” የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት

44

ባሕር ዳር: መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ምዝገባ ማድረጋቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን በ2015 ዓ.ም የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራሔል አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የበጀት ዓመት 25 ሚሊዬን ዜጎች መታወቂያውን እንዲያገኙ እየተሠራ ነው።

አሁን ላይ ከሦስት ሚሊዬን በላይ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት ምዝገባ ማድረጋቸውን ገልጸው የምዝገባው ሥራ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የዲጂታል መታወቂያው የቀበሌ መታወቂያን ለመተካት ሳይሆን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሰጪዎች የግለሰቦችን ማንነት እንዲለዩ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ብሔራዊ መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ መሆኑን ተናግረው የመታወቂያው ዓላማ ዜጎች የማንነት ማረጋገጫ በማሳየት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ነው ብለዋል።

በቀጣይ ሁኔታዎችን በማየት የዲጂታል መታወቂያና የቀበሌ መታወቂያ በተመጋጋቢነት ሊሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ነው ያብራሩት።

የብሔራዊ መታወቂያ ዜጎች ጊዜና ቦታ ሳይወስናቸው በኤሌክትሮኒክስ አማራጭ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 90 ሚሊዬን ዜጎችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መታቃዱን ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እቅዱ የተፈናቀሉ ዜጎች፣ ሰብአዊ እርዳታ የሚያሻቸውና ሌሎች ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ የማይችሉ ዜጎችን ታሳቢ ማድረጉ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!