ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን የልማት ስኬቶች በ5ኛው የተመድ ዓለም አቀፍ የአዳጊ ሀገራት ጉባዔ ላይ አካፈለች

48
ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን የልማት ስኬቶች በ5ኛው የተመድ ዓለም አቀፍ የአዳጊ ሀገራት ጉባዔ ላይ አካፍላለች፡፡
ኢትዮጵያ በግብርናው ክፍል ኢኮኖሚ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች በኳታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው እና በአዳጊ ሀገራት ላይ በሚመክረው 5ኛው የተመድ ጉባዔ ላይ ያካፈለችው በፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ አማካኝነት ነው።
ዶክተር ፍጹም አሰፋ በመድረኩ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ በስንዴ ምርታማነት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እና በተለያዩ የልማት መሥኮች ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች አቅርበዋል፡፡
አዳጊ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን መሰረት አድርገው ሲሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ መሆኗንም አስረድተዋል፡፡
በአዳጊ ሀገራት ላይ የሚደርሱ ፈተናዎችን ለመቋቋም የዓለም አቀፍ አጋሮችን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጥ አሥፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
በሥራ ላይ ያለው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ትርጉም ያለው ምላሽ መሥጠት እንዳልቻለም ዶክተር ፍጹም መጥቀሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚስተዋለው አለመረጋጋት ገፈት ቀማሽ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ታዳጊ ሀገራት የዓለም አቀፉን ገበያ ለመቀላቀል ፈተና እንደሆነባቸው እና ጥረታቸው ብዙም ፍሬያማ ውጤት እንዳላስገኘ አስረድተዋል።
በመሆኑም ያደጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የዕዳ እፎይታን በመስጠት የልማት እና የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጎልበት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!