አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በቻይና የብሔራዊ ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ።

12

ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ ከሚገኙት በቻይና የብሔራዊው ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰንና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በፈረንጆቹ ከ1970 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በጠነከረ ወዳጅነትና አጋርነት መዝለቁ ታሪካዊ ነው ተብሏል፡፡

ሀገራቱ ያላቸው ግንኙነት ከፍ ወዳለ የመንግሥታት ግንኙነትና አጋርነት መለወጡም ትልቅ ማሳያ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና መንግሥት የወሰዳቸው ጠቃሚ ልምዶች እንዳሉ አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

ለተማሪዎች ምገባ፣ ለወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለወጣት ተማሪዎች እየተሰጠ የሚገኘው ነጻ የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያን የእውቀት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ለእድገቷም ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰ በበኩላቸው÷ የኢትዮ ቻይና ግንኙነትና አጋርነት ቆየት ያለ መኾኑን አስታውሰዋል፡፡

ቻይናውያን በኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መሰማራታቸው የሀገራቱ ግንኙነት ነባር ብቻ ሳይኾን ቀጣይነት ያለው መኾኑን አስረጂ ከመኾኑም ባሻገር ሀገሪቷ ለውጪ ባለሀብቶችና ለኢንቨስትመንቶች ምቹ ስለመኾኗ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኝነት ለመከላከል ያለውን ጽኑ ፍላጎትና ተነሳሽነት መንግሥታቸው እንደሚደግፍም አስረድተዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የንግድ፣ የባሕል፣ የማኅበራዊ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ግንኙነቶች አሉ ተብሏል፡፡

ግንኙነቶቹን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው በመሥራት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን እልባት ለመስጠት ከስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡

የልኡካን ቡድኑ በቀጣይ ቀናትም ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያይ የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!