”ኅብረተሰቡ በመተባበር መብት እና ጥቅሙን ሊያስከብር ይገባዋል” የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጄስቲክስ ባለሥልጣን

22

ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መኾኑ ይታወቃል። ደረጃውን የጠበቀ መንገድ በበቂ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እጥረት፣ በዘርፉ የተሠማሩ አገልግሎት ሰጪዎች የሥነ ምግባር ችግር እና የተገልጋዩ ሕዝብ ቸልተኝነት እንዲኹም ተስፋ ቆራጭነት ለችግሩ ባለድርሻ መኾናቸውንም አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በአማራ ክልልም በቂ የትራንስፖርት አውቶቡሶች አለመኖር፣ ከተመን በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን፣ ተሳፋሪን ማመናጨቅና ማንገላታት በየዕለቱ የሚታይ ክስተት ከኾነ ውሎ አድሯል። በዚህም ኅብረተሰቡ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኝ አድርጎታል።

በከተሞችም ባጃጅ እና ታክሲዎች ትርፍ በመጫን፣ ከተመን በላይ በማስከፈል፣ የተሳፋሪን ክብር የሚነኩ መልዕክቶችን በመለጠፍ፣ ሕዝብን ለችግር ማጋለጣቸው እንደቀጠለ ነው አስተያየት ሰጪዎች የተናገሩት።

በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝብ በማጓጓዝ ዘርፉ ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩ መኖራቸውን የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጄስቲክስ ባለሥልጣን አሥታውቋል።

በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዳይሬክተር ደሳለኝ አዳነ ችግሩን ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ ወቅታዊው የሰላም ችግር እንቅፋት መኾኑን ገልጸዋል። የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን ምቹ ለማድረግ የሚሠሩ የግንዛቤ ፈጠራ እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ችግር ቢያጋጥምም በቀሪዎቹ ቦታዎች ግን እየተሠራ ነው ብለዋል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ እና ሥራው እንዳልቆመም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡም ታክሲ ሲጠቀምም ኾነ ረጅም ርቀት ሲጓዝ ከተመን በላይ ክፍያ፣ ትርፍ መጫን እና ሌሎች ሕገወጥ አገልግሎቶችን በጋራ ኾኖ በመቃወም እና በመከላከል መብቱን እና ጥቅሙን ማስከበር አለበት ሲሉ አሳስበዋል ዳይሬክተሩ።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!