ተቋማቱ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

34

ባሕር ዳር: መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የአማራ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ ስምምነት ፈጽመዋል።

ስምምነቱ የሥራ አመራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎትን መስጠት፣ የመሬት አሥተዳደርን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የዕውቀት ሽግግር ማካሄድ እና ሥልጠና መስጠትን ያካተተ መኾኑ ተጠቅሷል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ ክልሉ ባለፋት ጊዜያት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ማለፋን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም ያደሩ እና አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተደረገ ምርመራ ሕገወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራ፣ የሥራ አጥነት ችግር እንዲሁም የመሰረተ ልማትና መሰል ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ዲጂታላይዜሽን ዋነኛ መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በአማራ ክልል ስማርት ሲቲ፣ ንግድና ቱሪዝም ላይ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!