“ባለፉት 4 አመታት የወጪ ንግድ ዘርፉ በአማካይ 7 በመቶ እድገት አሳይቷል” የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

22

ባሕርዳር፡ መስከረም 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ባለፉት 4 አመታት የወጪ ንግድ ዘርፉ ላይ በትኩረት በመሰራቱ በአማካኝ 7 በመቶ ዉጤት ማስመዝገብ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ከወጪ ንግድ ዘርፎች ውስጥ የግብርና ዘርፍ በዋነኝነት ቡና፣ የቅባት እህሎችና አበባ እንዲሁም ጫት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸውም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የቡና እና አበባ ምርቶች ከታቀደው በላይ ትርፍ የታየባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልጾ፤ የማዕድን ዘርፉም ጥሩ የሚባል እድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁሟል። ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ ከማዕድን ዘርፉ በተለይ ወርቅ ወደ ውጭ በማቅረብ ዉጤት እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ለውጪ ገበያ እየቀረቡ ነዉ ያለው ሚኒስቴሩ በተጨማሪ ባለፉት 4 አመታት የአገልግሎት ወጪ ንግድ ላይ እድገት ታይቷል ብሏል፡፡

በአገልግሎት ዘርፍ በ2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 69 ቢሊዮን ዶላር ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን እንዲሁም በእቅዱ ማብቂያ አመት በ2015 ደግሞ 6.07 ቢሊዮን ዶላር ታቅዶ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ነው ያለው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!