“በ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር)

23

አዲስ አበባ: መስከረም 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ መትከል መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሐ ግበር በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ የጃጎ ተፋሰስ ላይ ተካሔዷል፡፡ በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “በ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባለው አንደኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ መትከል ችለናል ብለዋል። 2015 ዓ.ም ላይ በአፋር ክልል የተጀመረው የሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ተተክሎበታል ነው ያሉት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከብዙ ምክክር፤ ከብዙ የአዳራሽ ወግ ያለፈ የተግባር ሥራ ማሳያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በርካታ ዓለም አቀፍ የአየር ንበረት ለውጥ ጉባኤ ቢካሄድም መሠረታዊ የተግባር ለውጥ ማምጣት እና ማሳየት የተቻለው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኾነ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥኬት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ እና እድገት ለማምጣት የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል። ያሰብነውን እና ያቀድነውን ከማሳካት ጉዞ የሚያስቆመን አንዳችም ኃይል እንደማይኖር ያረጋግጣል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሽዋ ዞን ሎሜ ወረዳ በ195 ሔክታር መሬት ላይ በለማው የጃጎ ተፋሰስ ላይ ሲካሄድ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!