ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ልማት ማኅበር በትምህርት ቤቶች ግንባታ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል። አልማ የመማሪያ ክፍሎችን ገጽታ የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችንም እያከናወነ ይገኛል።
አልማ በደቡብ ጎንደር ዞን 330 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረጉን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ለአሚኮ ገልጿል።
330ዎቹ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በ74 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በ10 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ መካሄዱንም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ አልማ በጎ ፈቃደኛ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደጀን አከለ አልማ በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አልማ በ2014 ዓ.ም በ11 ትምህርት ቤቶች ላይ 44 የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ ያጠናቀቀ ሲኾን፤ በ2015 ዓ.ም በሥምንት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 29 ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ አጠናቋል ነው ያሉት፡፡
አቶ ደጀን አልማ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ ጥራት በመገንባት የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ምቹ እያደረገ እና ወላጆች ልጆቻቸውን ወደውና ፈቅደው ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ በማድረግ በኩል ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የአልማ አስተባባሪዎች እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የግንባታ ሥራው በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ድጋፍ እና አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዞኑ የጉና በጌምድር ወረዳ የአልማ ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አበራ ኢሳያስ አልማ በ2015 ዓ.ም በስድስት ትምህርት ቤቶች ላይ 24 መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል፡፡ አልማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው ባለፉት ዓመታትም አልማ በ12 ቀበሌዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የመማሪያ አካባቢዎችን ምቹ ማድረጉንም አንሰስተዋል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመትም ግንባታ የሚካሄድባቸውን ትምህርት ቤቶች ልየታ እየተካሄደ እና የሃብት ማሰባሰብ ሥራው መቀጠሉንም አቶ አበራ ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን አልማ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኀላፊ መሣፍንት ልብሴ በዞኑ በሚገኙ 84 ትምህርት ቤቶች ላይ ሁለት ቤተ-መጽሐፍት፣ ሁለት ቤተ ሙከራ እና 330 መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ የተጨማሪ መማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ በ74 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በ10 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ 84 ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች ተገንብቶላቸዋል፡፡
ለመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ ማሕበረሰቡ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት ቁሳቁስ እና 14 ሚሊየን ብር የሚገመት የጉልበት ድጋፍ አድርጓል ተብሏል፡፡ ለግንባታው ከማሕበረሰቡ የቁሳቁስ እና የጉልበት ድጋፍ በተጨማሪ 214 ሚሊየን ብር ገደማ ወጪ መደረጉንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ አልማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የመማር ማስተማር ሥራው በመደገፍ በኩል ከማኅበረሰቡ ጋር ተግባብቶ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኹሉም ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ኀላፊነት እየተወጡ መኾኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ የመማሪያ ክፍሎች መሻሻል የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ድግግሞሽ በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ድርሻው ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ትውልድን በአግባቡ ለመቅረጽ የኹሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት አቶ መሳፍንት አልማ ስትራቴጅክ እቅዱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!