በደሴ ከተማ ከ64 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታና ጥገና ሥራ ተካሄደ።

36

ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ ከ64 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አንድ አዲስ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታና ጥገና መካሄዱን የከተማው አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

ግንባታውና የጥገና ስራው የተካሄደው በመንግስት፣ በአለም ባንክ ድጋፍና በኅብረተሰብ ተሳትፎ መሆኑንም ገልጿል፡፡

በመምሪያው የትምህርት ልማት ስታትስቲክስ ትንተና፣ ዕቅድ ዝግጅትና ሀብት ማፈላለግ ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡

ከዚህም በከተማው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የገጠመውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለማቃለል 10 መማሪያ ክፍሎችንና ሌሎች ተጓዳኝ መገልገያዎችን ያካተተ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 30 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የተጎዱና በአገልግሎት ብዛት ያረጁ አምስት የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርት ቤቶች አምስት ተጨማሪ ህንጻዎችን በመገንባት 60 አዲስ መማሪያ ክፍሎች ለትምህርት ዘመኑ ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል።

ለአዲሱ ትምህርት ቤትና ለተጨማሪ ህንጻዎች ግንባታ ከመንግስትና ከአለም ባንክ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ያመለከቱት ቡድን መሪው፤ በሁለት ፈረቃ ከ6 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚያስችሉ አስረድተዋል።

የመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ ግንባታዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 356 ነባር መማሪያ ክፍሎች፣ 92 ቤተ ሙከራና ቤተ መጽሐፍት፣ 110 የቴክኖሎጅ ማዕከልና አስተዳደር ቢሮዎች፣ ከ2 ሺህ 300 በላይ ወንበርና ሌሎችን በመጠገን ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።

ከደሴ ነዋሪዎች መካከል አቶ አራጋው አሊ በሰጡት አስተያየት፤ የተገነቡ አዲስ መማሪያ ክፍሎች ልጆቻችን በተሻለ ደረጃ መማር እንዲችሉ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበሩ መማሪያ ክፍሎች ያረጁ በመሆናቸው ለመማር ማስተማር ስራው አመቺ እንዳልነበሩ አሰታውሰው አሁን ምቹ በመደረጋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

”በአዲስ የተገነባልን ህንጻ አዲሱን የትምህርት ዘመን በደስታ እንድንጀምር ያደርገናል” ያለው ደግሞ በትግል ፍሬ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ከድር የሱፍ ነው፡፡

በደሴ ከተማ አስተዳደር በ2016 የትምህርት ዘመን በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!