ባሕርዳር፡ መስከረም 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሁለት ቀናት በኩባ ሀቫና ሲካሄድ የቆየው የቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ ተጠናቋል።
ጉባኤው በማጠናቀቂያው የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍላጎት የሚያስተናግድ እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። በተናጠል የሚጣሉ ማዕቀቦችና ኃይልን መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ እርምጃዎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ልማት ለውጦችን እንደሚያስተጓጉሉም ገልጸዋል።
በደቡብ-ደቡብ የትብብር መድረክ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ ፈጠራን ለማሳደግና ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እየተገበረች ባለው የዲጂታል ስትራቴጂ ለሰፊው ማኅበረሰብ ሰፊ ጥቅሞችን መስጠት የሚችል ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር ራዕይ ሰንቃ እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ስትራቴጂውን በመተግበር አበረታች ውጤቶችን እያገኘች መሆኑን ነው አቶ ደመቀ ያስረዱት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ እና ከሌሎች የአገሪቷ ባለስልጣናት እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ኢንገር አንደርሰን ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ኢትዮጵያዊ በጉባኤው በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ስኬታማ ሥራ ማከናወኗም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!