ባሕርዳር፡ መስከረም 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱን የትምህርት ዘመን ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በአማራ ክልል የ2016 የትምህርት ዘመን ለማስጀመር የሚያስችል የተማሪዎች ምዝገባን ጨምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
በክልሉ ባለፈው የትምህርት ዘመን የነበረውን የመጽሐፍት እጥረት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ እየሩስ መንግሥቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የትምህርት ግብዓቶች መካከል መጽሐፍ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን ተከስቶ የነበረውን የመጽሐፍ እጥረት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን መጻሕፍት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት እንዲታተሙ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ እየሩስ ከታተሙት መጻሕፍት መካከል 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት መጽሐፍት እየተሰራጩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ቀድሞ የታተሙ መጽሐፍት ባለፉት ጊዜያት መሰራጨታቸውን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን መጻሕፍት ወረዳ ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ወረዳዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት እንደሚያሰራጩ ነው የተናሩት፡፡
በክልሉ የሚገኙ የክዘና ማዕከላት የመጽሐፍት ስርጭቱን ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው ተብሏል፡፡ መጽሐፍቱን የዓመቱ የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ከመጀመሩ አስቀድሞ ወደ ትምህርት ቤቶች ለማድረስ እየተሠራ መሆኑንም ወይዘሮ እየሩስ አስታውቀዋል፡፡ ተጨማሪ 3 ሚሊዮን መጽሐፍትን ለማሳተም በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ታትመው በስርጭት ላይ ያሉ መጻሕፍት የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍት መሆናቸውን የነገሩን ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጽሐፍት በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት የሚታተሙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሚያቀርበው የመጀመሪያ ደረጃ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መጽሐፍት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን የመጽሐፍት ችግር ፈታኝ እንደበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ ችግሩ በተያዘው የትምህርት ዘመን እንደሚቀርፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የሰላም እጦት በሌሎች ተቋማት ላይ እንዳሳደረው ጫና ሁሉ በትምህርት ዘርፉም ጫና መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት አንድ የመጻሕፍት ክዘና ማዕከል እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!