ጅግጅጋ: ኅዳር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሱማሌ ክልል ጉብኝት እያደረገ ያለው የጋዜጠኞች ቡድን የጅግጅጋ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመልክቷል።
የክልሉን ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን በሱማሌ ክልል ውኃ ቢሮ የመጠጥ ውኃ ዳይሬክተር አብዲ ከድር አብዱላሂ መሃመድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ የውኃ አገልግሎት ሽፋን ከ5 ዓመት በፊት 19 በመቶ የነበረ ሲኾን አሁን ወደ 43 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ሲሉም ገልጸዋል። በክልሉ 13 አነስተኛ እና ትላልቅ የውኃ ግድቦች ተሠርተው የመጠጥ ውሃ ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በጅግጅጋ ከተማ ከ5 አመታት ወዲህ 8 ጉድጓዶች ተቆፍረው በቀን 10 ሺህ ሜትር ኪዩብ የነበረውን የከተማዋ የውኃ አቅርቦት በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል ዳይሬክተሩ።
የከተማዋ አጠቃላይ የውኃ ፍላጎት 40 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ሲኾን አሁን ላይ 50 በመቶውን ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ ሥራ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ፍላጎቱ መቶ በመቶ እንደሚሟላ አቶ አብዲ ጠቁመዋል።
በክልሉ ሰላም የሰፈነ መኾኑ እና መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ ለልማት መሥራታቸው ለውጤት እንዳበቃም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ – ከጅግጅጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!