“በሩብ ዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 200 ባለሃብቶች ፍቃድ አግኝተዋል” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

12

ጎንደር: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጎንደር ቀጣና ከሚገኙ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊዎቾ ጋር የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም እና የእቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል። በአማራ ክልል ባለው ሰፊ እና ሊለማ የሚችል ጸጋ መጠቀም ባለመቻሉ በክልሉ የሥራ አጥ ቁጥሩ ለመጨመሩ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል፡፡ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት በሰላም እጦት እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች እየተፈተነ አሁን ካለበት ደርሷል፡፡

በባሕርዳር፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጎንደር እና በመሳሰሉት ዋና ዋና ከተሞች ሰፊ የኢንዱስትሪ መንደር ያላቸው በመኾኑ ተጠቁሟል። እነዚህ መንደሮች በሙሉ አቅም ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር እንደመሆኑ ጠበቅባቸውም ተነስቷል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሃንስ አማረ እንዳሉት “በሩብ ዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 200 ባለሃብቶች ፍቃድ አግኝተዋል” ብለዋል። ከ450 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎ የሥራ እድል ለመፍጠር በእቅዳቸዉ እንዳካተቱም ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ በክልሉ የጸጥታ ችግር የተከሰተ ቢኾንም ባለሃብቶች በኢንቨስትመንቱ ላይ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾኑን የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በዘርፉ ላይ ባለሃብቶች በትጋት እየሠሩ ቢኾንም አበዳሪ ተቋማትና የመሬት ካሳ ክፍያ መጋነን ኢንቨስትመንቱ ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋት እንደኾነውም ተገልጿል፡፡ ከመሬትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ይገባልም ተብሏል።

ከዉጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ዉስጥ ለመተካት በተደረገዉ ጥረትም ከ28 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉም በመድረኩ ተገልጿል። ወደ ዉጭ ከተላኩ ምርቶች ደግሞ ከዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መገኘቱን ተነግሯል፡፡

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!