“በሁለት ቀናት ከ450 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሰዎች የኮሌራ በሽታ ክትባት ተደራሽ ተደርጓል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

13

ባሕር ዳር: መስከረም 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የኮሌራ በሽታ ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናትም ለ450 ሺህ ዜጎች ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተስብ ጤና አደጋዎች ማሳለጫ ማዕከል ቡድን መሪ አሞኘ በላይ እንዳሉት በአማራ ክልል ለኮሌራ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ክትባቱ ከመስከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ነው፡፡

ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ብርሃን ከተሞችን ጨምሮ በቋራ፣ መተማ፣ ደራ፣ ምሥራቅ ደምቢያ፣ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ሞጃና ወደራ ወረዳዎች ከመስከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል። ክትባቱ እስከ መስከረም 10/2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

አንድ ዓመት እና በላይ ለኾናቸው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችም ክትባቱ ተደራሽ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ ክትባቱ መሰጠት ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ለ453 ሺህ 990 ሰዎች ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡

ቡድን መሪው ክትባት ከመስጠት ጎን ለጎን መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የግል፣ የአካባቢ፣ የምግብ ንጽህናን እና ውኃን አክሞ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ክትባቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን ውጤታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!