ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።

76

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ደመቀ በቻይና ዋና የኢንቨስትመንት መናኸሪያ በሆነችው ጓንዦ ከተማ ዛሬ በተካሄደ የኢንቨስትመንት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን የተሻለ የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል፡፡

ከሶስት መቶ የሚበልጡ ታዋቂ በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ኢነርጂ፣ ፋርማሲዩቲካልና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በተሳተፉበትና የጓንዶንግ ግዛት ዋና ከተማ ባስተናገደችው መድረክ ላይ አቶ ደመቀ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በኢኮኖሚው መስክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የጓንዶንግ ግዛት የንግድ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዣዎ ቺን በበኩላቸው በጓንዶንግ በማኑፋክቸሪንግ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በማዕድን፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና ሌሎችም ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገብተው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በቻይና የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው በበኩላቸው የኢኮኖሚ መድረኩ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

የጓንዶንግ ግዛት አጠቃላይ ምጣኔ ሃብት (GDP) ከ1 ነጥብ 8 ትሪሊያን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሲሆን ይህም በቻይና ካሉ 32 ግዛቶች ቀዳሚ እንደሚያደርገውና አጠቃላይ የወጪ ምርቱም ከአንድ ትሪሊዬን የአሜሪካ ዶላር በላይ መድረሱ ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከተለያዩ ከፍተኛ አቅም ካላቸው ኩባንያዎች ሃላፊዎችና መስራቾች ጋር በተናጠል ተገናኝተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ኢንዲያደርጉ በመጋበዝ አበረታተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!