“ለሰላምና ለመልካም ነገር የሚደረጉ ጉዳዮች ያለከልካይ ይፈጸማሉ” ብርጋዴር ጀኔራል ማርየ በየነ

140

ጎንደር: መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰላም ምልክት የፍቅር ተምሳሌት የኾነው የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች በበዓሉ አከባበር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም ለሰላም በሯ ክፍት ነው ፤ ቀዳሚም ተግባሯ ነው ያሉት የሃይማኖት አባቶች ለ2016 ዓ.ም የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ዝግጅት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ብቻ ዓላማ አድርገው መሰብሰብ የሚፈልጉ ወጣቶች በመኖራቸው ኮማንድ ፖስቱ ለቀና ሃይማኖታዊ ተግባር ሲባል ሊፈቅድና የጊዜ ማሻሻያ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የመከላከያ ሠራዊት 504ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ማርየ በየነ “ለሰላምና ለመልካም ነገር የሚደረጉ ጉዳዮች ያለከልካይ ይፈጸማሉ”ብለዋል።

ብርጋዴር ጀኔራሉ የመስቀልን በዓል በሰላምና በተሳካ ኹኔታ ማክበር ለአካባቢውና ለቀጣይ ሥራዎች መልዕክቱ ከፍ ያለ እንደኾነ አንስተዋል።

መስቀልን በሰላም ማክበር ለቀጣዩና ታላቁ የጥምቀት በዓል ስንቅ ከመኾኑም ባሻገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ርዝማኔም ሊያሳጥረው ይችላል ብለዋል።

በውይይቱ ወጣቶችን ያሳተፉ ሥራዎች ይከናወናሉም ነው የተባለው።

ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!